
“ለአረንጓዴ ኢትዮጵያ” በሚል መሪ ቃል በኩባንያችን ደረጃ 500 ሺህ ችግኞችን ለመትከል በተያዘው ዕቅድ መሰረት በዛሬው ዕለት በመላው የሃገራችን ክፍሎች በሚገኙ የኩባንያው ጽ/ቤቶች የችግኝ ተከላ መርሃ-ግብሮችን በይፋ አስጀምሯል፡፡ ይህም ኩባንያችን በአረንጓዴ ልማት ዘርፍ የማህበረሰባችን ዘላቂ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ስትራቴጂ ነድፎ (sustainable strategy) ከሚያከናውናቸው ቁልፍ የልማት ዘርፎች መካከል አንዱ ነው፡፡
ይህንን ተከትሎ በ7ኛው ዙር አገር አቀፍ አረንጓዴ አሻራን የማሳረፍ ዘመቻ መርሃ ግብር ወደ 500 ሺህ የሚደርሱ ችግኞችን ለመትከል ኩባንያችን በኮርፖሬት፣ በዞን እና ሪጅን ደረጃ ከ12,000 በላይ የኩባንያው ሠራተኞችን በማሳተፍ በአዲስ አበባ ውበት እና አረንጓዴ ልማት ቢሮ በተመረጡ የተከላ ሳይቶች የችግኝ ተከላ ዘመቻ አካሂዷል፡፡
በዚህም መሰረት ኩባንያችን በኮርፖሬት እና ዞን ደረጃ እንጦጦ እና ሀምሊን ፊስቱላ ቅጥር ግቢ (አሸዋ ሜዳ) አካባቢ በተዘጋጁ ቦታዎች የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ያከናወነ ሲሆን፣ የኩባንያው 18 ሪጅኖች ደግሞ ሪጂኖቹ ከሚገኙባቸው መስተዳድሮች በተረከቧቸው ቦታዎች ላይ የችግኝ ተከላ ዘመቻ አካሂደዋል፡፡
ኩባንያችን በሰባተኛው ዙር የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር በመላ ሀገሪቱ 500,000 ሺ ችግኞችን ለመትከል ከ57 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት የመደበ ሲሆን፣ ባለፉት ተከታታይ ስድስት ዓመታት በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች በሚገኙ 805 አካባቢዎች ከ4.3 ሚሊዮን በላይ ችግኞች በመትከል አረንጓዴ አሻራውን ማኖር ችሏል፡፡ በዚህም በአማካይ ከ82.5 በመቶ በላይ ችግኞችን በማፅደቅ የተራቆቱ አካባቢዎችን አረንጓዴ በማልበስ በረሃማነትንና ድርቅን በልምላሜ ለመቀየር የበኩሉን ጥረት ከማድረጉም በላይ ከ23ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ጊዜያዊ የስራ ዕድል መፍጠር ችሏል፡፡
ኩባንያችን ከኮኔክቲቪቲ አገልግሎት ባሻገር ዓለም የደረሰበትን የዲጂታል ቴክኖሎጂን ለማህበረሰባችን ተጠቃሚ እንዲሆን በማድረግና በዲጂታል ፋይናንስ ዘርፍ ጉልህ አስተዋጽኦ በማድረግ የዲጂታል ኢትዮጵያን ራዕይ እውን የማድረጉን ጉዞ አጠናክሮ እየገፋበት ሲሆን፣ ከዚሁ ጎን ለጎን የማህበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣትም በበርካታ ዘርፎች ከፍተኛ ድጋፍ እያደረገ ይገኛል፡፡
ከኩባንያችን የማህበራዊ ኃላፊነት ፖሊሲ ዋና ዋና አምዶች (Pillars) መካከል አንዱ ለአካባቢ ጥበቃ እና ልማት ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደመሆኑ መጠን ዘመን ተሻጋሪ አስተዋፅኦ እያበረከተ ይገኛል፡: ለአብነትም ኩባንያችን የዘንድሮውን ጨምሮ ባለፉት ሰባት ተከታታይ ዓመታት ለአረንጓዴ አሻራ እና የኢኮ ቱሪዝም ፕሮግራሞች ከ1.03 ቢሊየን ብር በላይ መዋለ ንዋዩን አፍስሷል፡፡
በተጨማሪም ኩባንያችን ሀገራችን ወደ አረንጓዴ ኢኮኖሚ የምታደርገውን ግስጋሴ በዘላቂነት ለመደገፍ የሚያስችሉ ቀጣይነት ያላቸው (future-ready) መሠረተ ልማቶችን በመገንባት ላይ የሚገኝ ሲሆን፣ ለአብነትም በቅርቡ በመዲናዋ ተግባራዊ የተደረጉት እና ወደ ከባቢ አየር የሚለቀቀውን ካርቦንዳይ ኦክሳይድ መጠን በእጅጉ ለመቀነስ የሚያስችሉ የኤሌክትሪክ መኪና ባትሪ መሙያ ጣቢያዎች እንዲሁም በበርካታ የኔትዎርክ ሳይቶች የሀይል አቅርቦት እጥረትን ለመተካት ጥቅም ላይ ይውል የነበረውን የነዳጅ ሀይል በፀሐይ ኃይል (solar) የመተካት ስትራቴጂዎች ይጠቀሳሉ፡፡
ሃገራችንን ለ131 ዓመታት በቁርጠኝነት በማገልገል ላይ የሚገኘው ኩባንያችን፣ የሀገራችንን ሁለንተናዊ እድገት ለመደገፍና የአስቻይነት ሚናውን ለመጫወት በየጊዜው አዳዲስ አገልግሎቶችን እና ቴክኖሎጂዎችን ከማቅረብ ባሻገር ለማህበረሰባችን እና ለሃገራችን ፋይዳ ያላቸው ልዩ ልዩ ፕሮግራሞችን በመቅረጽ፣ ሃገራዊና ማህበራዊ የጥምር ኃላፊነቱን መወጣቱን አጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል፡፡
ሐምሌ 24 ቀን 2017 ዓ.ም
ኢትዮ ቴሌኮም