ኢትዮ ቴሌኮም እና የኢትዮጵያ የመድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት ስማርት ዲጂታል የጤና አቅርቦት ሰንሰለት ሶሉሽን ለመተግበር የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት አደረጉ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 8 ቀን 2018 ዓ.ም፣ የሀገራችን ዲጂታል ሶሉሽኖች አቅራቢ የሆነው ኢትዮ ቴሌኮም፣ በመላ የሀገራችን ክፍሎች መድኃኒቶችን እና የህክምና ቁሳቁሶችን የመግዛት፣ የማከማቸት እና የማከፋፈል ኃላፊነት ከተሰጠው ብሔራዊ ኤጀንሲ፣ የኢትዮጵያ የመድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት (EPSS) ጋር ስማርት የዲጂታል ጤና አቅርቦት ሰንሰለት ሶሉሽን ለማቅረብ የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት አድርጓል፡፡ ይህ ስምምነት በዋናነት በመላ ሀገሪቱ የመድኃኒቶች እና የህክምና ዕቃዎች ፍሰትን የሚያቀላጥፍ ዘመናዊ፣ አስተማማኝ እና በመረጃ የተደገፈ የአቅርቦት ሰንሰለት ሶሉሽን ለመንደፍ እና ለመዘርጋት ያለመ ነው።

ኩባንያችን በሶስት ዓመቱ “ኢትዮ ቴሌኮም ቀጣዩ አድማስ፡ ዲጂታል እና ከዚያ በላይ 2028 ስትራቴጂ” በመመራት፣ በዘመናዊ ኮኔክቲቪቲ እና የፈጠራ ኢንተርፕራይዝ ሶሉሽንስ አማካኝነት በሀገራችን ሁለገብ እድገትን ለማረጋገጥ በቁርጠኝነት እየሰራ ይገኛል። ይህ በዛሬው ዕለት ከኢትዮጵያ የመድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት ጋር ያደረግነው ስምምነት የኢትዮጵያን ብሔራዊ ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን እውን ለማድረግ ከሚያስችሉ ሴክተር-ተኮር ዲጂታል ሶሉሽኖች መካከል አንዱ ነው።

ስማርት የአቅርቦት ሰንሰለት ሶሉሽን

በዚህ የትብብር ማዕቀፍ፣ ሁለቱ ተቋማት በመላ ሀገሪቱ የመድኃኒቶች እና የህክምና ዕቃዎች ፍሰትን የሚያቀላጥፍ ዘመናዊ፣ አስተማማኝ እና በመረጃ የተደገፈ የጤና አቅርቦት ሰንሰለት ሶሉሽን በጋራ በመንደፍ ተግባራዊ የሚያደርጉ ይሆናል፡፡

የዲጂታል ሶሉሽኖች የሚያካትቷቸው ቁልፍ ጉዳዮች:-

  • አንድ ወጥ አሰራርና ቁጥጥር:በአንድ ማዕከል ፕላትፎርም አማካኝነት አፋጣኝ የኦፕሬሽናል መረጃ (data) እና የቅድመ አደጋ ማንቂያዎችን በመጠቀም ፈጣን ውሳኔ እና ለሚከሰት አደጋ ቀልጣፋ ምላሽ ለመስጠት ያስችላል።
  • በሰው-ሰራሽ አስተውሎት የሚደገፍ የደህንነት ጥበቃ:በዘመናዊ የቪድዬ ትንተና (የፊት ገጽታና የተሽከርካሪ ሰሌዳ ልየታ እና የባህሪ ትንተና) በመጠቀም አስተማማኝ የንብረትና ደህንነት ጥበቃን ለማረጋገጥ፣
  • ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችና የጎብኚዎች አስተዳደር:የባዮሜትሪክ ናሙናዎችን በመጠቀም ግምጃ ቤትና ቢሮዎችን በዘመናዊ ስማርት የጎብኚዎች የማንነት መለያ እና የምዝገባ ሥርዓት ለመቆጣጠር፣
  • የኦፕሬሽን ልዕቀት:የምሽት እንቅስቃሴን ጨምሮ የአሽከርካሪዎችን እና የግምጃ ቤት እንቅስቃሴዎችን ለመቆጣጠር የሚያስችሉ እንዲሁም የነዳጅ መጠን ልየታን፣ የበር ደኅንነት ሁኔታን፣ የጭነት ማከማቻ አቅምን ለመለየት የሚያስችል የስማርት ቪድዮ ትንተና፣
  • አስተማማኝ መሰረተልማት:አስተማማኝ የኢንተርኔት ኮኔክቲቪቲ፣ ለዋና ማዕከላት  የመጠባበቂያ (UPS) የኃይል አቅርቦት፣ ዘመናዊ የቁጥጥር ክፍሎች እንዲሁም በአንድ ጊዜ እስከ 8 ተሽከርካሪዎችን ማስተናገድ የሚችል የኤሌክትሪክ መኪና መሙያ ጣቢያን ያካተተ፣

 የሚያስገኘው ውጤት:-

  • ፈጣንና በመረጃ የተደገፈ ውሳኔን በመስጠት የኢትዮጵያ የመድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት አሰራርን ለማቀላጠፍ፣
  • ዘመናዊ አሰራርን በመተግበርና የቅድመ ጥንቃቄን በማድረግ የስራ ጫናን ለመቀነስ፣
  • የመድኃኒት ቁጥጥር ለማሻሻል እና የንብረት ቆጠራ ሥርዓትን ትክክለኛነት ለማረጋገጥ፣
  • ጠንካራ የሃብት ደህንነት ቁጥጥር ለማድረግ እና የሕግ ተገዢነትን ለማረጋገጥ፣
  • ከግምዥ ቤት ጀምሮ እስከ ተጠቃሚው ያለውን የመድኃኒት ስርጭት የአገልግሎት ጥራትን እና ፍጥነትን ለማረጋገጥ የሚሉት ይገኙበታል፡፡

ይህ ትብብር የኢትዮ ቴሌኮም  የሶስት ዓመት “ቀጣዩ አድማስ፡ ዲጂታል እና ከዚያ በላይ 2028 ስትራቴጂ” ዋና ምሰሶዎች ውስጥ አንዱንና በዲጂታል ሶሉሽን አቅርቦት ዙሪያ የሚያከናውናቸው ስራዎች ዋናው ማሳያ ሲሆን፣ ይህም ተቋማት አሰራራቸውን እንዲያዘምኑ፣ ምርታማነታቸውን እንዲጨምሩ እንዲሁም ዜጎችን በላቀ ፍጥነትና ጥራት እንዲያገለግሉ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል” ብለዋል፡፡

ኩባንያችን በጤና አጠባበቅ፣ ሎጂስቲክስ፣ ፋይናንስ፣ ትምህርት እና ሌሎች ወሳኝ ዘርፎች ውስጥ የተሰማሩ አጋሮቹን ከዘመኑ ጋር የዘመኑ፣ አስተማማኝ እና ለወደፊት ዝግጁ በሆኑ የዲጂታል ቴክኖሎጂዎች ለማስታጠቅ ያለውን እምቅ አቅም በቁርጠኝነት እየተጠቀመ ይገኛል፡፡ በተለይም ሴክተር -ተኮር የዲጂታል ፈጠራዎችን በማቅረብ ረገድ፣ የኢትዮጵያ ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ግንባር ቀደም ሆኖ እየመራ የሚገኝ ሲሆን፣ ይህም የመንግስትና ቢዝነሶች አሰራርን እንዲሁም አጠቃላይ የማህበረሰባችን አኗኗር ዘይቤን ለማዘመን እና ቀጣይነት ያለው ለውጥ ለማምጣትና በጎ ተፅዕኖ ለማሳደር የላቀ አስተዋጽኦ ይኖረዋል፡፡

ኢትዮ ቴሌኮም

መስከረም 8 ቀን 2018 ዓ.ም.

Share This Post:

Share on facebook
Share on telegram
Share on twitter
Share on linkedin
Share on reddit
Share on pinterest
Share on tumblr
Share on whatsapp

Follow Us

Recent Posts

Archives