ኩባንያችን በሩዋንዳ ስማርት ትምህርት ሶሉሽን ለመተግበር የሚያስችል የመግባቢያ ሰነድ ተፈራረመ
ኢትዮ ቴሌኮም በሩዋንዳ በመካሄድ ላይ በሚገኘው 2025 ኪጋሊ የሞባይል ዓለም አቀፍ ኮንግረስ (MWC) ላይ በክቡር ዶ/ር ጆሴፍ ንሴንጊማና የሩዋንዳ የትምህርት ሚኒስትር የተመራውን ልዑካን ቡድን እና ከFEWA (Future of Education & Work in Africa) የተወከሉትን ልዑካን አጋሮቻችን እ.አ.አ. ኦክቶበር 23 ቀን 2025 በኪጋሊ አውደርዕያችን ላይ ጉብኝት በማድረጋቸው ታላቅ ኩራት ይሰማናል፡፡
የኩባንያችን አመራሮች ፈጠራ ላይ የተመሰረቱ አዳዲስ የስማርት የትምህርት ሶሉሽኖችንን አስመልክቶ ገለጻ ያደረጉ ሲሆን፣ በዚህም ክቡር ዶ/ር ንሴንጊማና የተሰማቸውን ከፍተኛ አድናቆት ገልጸዋል፡፡ ክቡር ሚንስትሩም አፍሪካ ይህንን የላቀ ዲጂታል ሶሉሽን ማዕቀፍ በመጠቀም የትሩፋቱ ተቋዳሽ መሆን አለባት ብለዋል፡፡
ይህን ተከትሎም ኩባንያችን እና FEWA ወሳኝ የሆነ የመግባቢያ ስምምነት (MoU) የተፈራረሙ ሲሆን፣ ይህ የመግባቢያ ስምምነት በሩዋንዳ እና በመላው አፍሪካ ስማርት ትምህርትን በጋራ ለማሳካት እና በትብብር በዘርፉ ትርጉም ያለው ለውጥ ለማምጣት ያለንን የጋራ ቁርጠኝነት የሚያጠናክር ይሆናል።
ይህ ስትራቴጂያዊ አጋርነት “ቀጣዩ አድማስ፡ ዲጂታልና ከዚያም ባሻገር 2028 ስትራቴጂ”ን ወደፊት ለማራመድ የተወሰደ ተጨባጭ እርምጃ ሲሆን፣ ይህም ኩባንያችን እና FEWA በጋራ በዲጂታል ሶሉሽኖች ረገድ ቀጠናዊ ትብብር ለመመስረት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል፡፡ ይህም ሁሉን አቀፍ እና በሰው ሰራሽ አስተውሎት ዝግጁ የሆነች፣ የዲጂታል አካታችነትን እና የፈጠራ ዕድገትን ያጠናከረች አፍሪካን እውን ለማድረግ የላቀ ሚና ይጫወታል፡፡


