ኩባንያችን ከኮኔክቲቪቲ አገልግሎት ባሻገር የሀገራችንን ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ስነምህዳርን የሚቀይሩ፣ ተቋማዊ አሰራርን የሚያዘምኑ እና የዜጎቻችንን የዕለት ተዕለት የአኗኗር ዘይቤን የሚያሻሽሉ ዘመኑ ያፈራቸውን ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን እና ዲጂታል ሶሉሽኖችን በቁርጠኝነት በማቅረብ እና በሰፊው ተደራሽ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ በተለይም የዲጂታል ሶሉሽኖችን ተደራሽነት በማስፋት የፋይናንሺያል አካታችነትን እና የሀገራችን ሁለንተናዊ እድገት ለማረጋገጥ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን በማከናወን የዲጂታል ኢትዮጵያን ጉዞ በማፋጠን ረገድ ቁልፍ ሚና እየተጫወተ ይገኛል፡፡
ኩባንያችን በዛሬው ዕለትም ከኦሮሚያ ግብርና ቢሮ ጋር በመተባበር በግዙፍ መረጃ የታገዘ የተቀናጀ ግብርና እሴት ሰንሰለት ለማቅረብ የሚያስችል (Agriculture Value Chain Big Data Platform Solution) ስምምነት አካሂዷል፡፡ ይህም በግዙፍ መረጃ ፕላትፎርም ሶሉሽን (Big Data Platform Solution) በመታገዝ የኦሮሚያ ግብርና እሴት ሰንሰለት (Oromia Agriculture Value Chain) ምርታማነትን፣ ቅልጥፍናን፣ ጥራትን፣ ትርፋማነትን፣ የገበያ ትስስርን እና የግብርናውን ዘርፍ የእሴት ሰንሰለት በዘላቂነት ለማዘመን ጉልህ ሚና ይኖረዋል።
ስምምነቱ በግብርናው ሂደት ውስጥ ያሉትን ሁሉንም ባለድርሻ አካላት እና ተዋንያን ማለትም ገበሬዎችን፣ በግብርናው ዘርፍ የተሰማሩ የተለያዩ ሴክተሮችን፣ የግብርና ግብዓት አቅራቢዎችን እና የተለያዩ ኢንተርፕራይዞችን፣ አከፋፋዮችን እና ቸርቻሪዎችን በማስተሳሰር የመንግሥትን እና የግሉን ዘርፍ ጥረቶች ለማዋህድ ከማስቻሉም ባሻገር ምርትን በማሻሻል፣ ሀብትን በብቃት ማስተዳደር፣ ተባዮችንና በሽታዎችን በመቆጣጠር፣ የገበያ ተደራሽነትን በመደገፍ፣ ዘላቂ ልማትን በማጎልበት እንዲሁም በመረጃ ላይ የተመሰረተ ፈጠራን በማምጣት የክልሉን የግብርና እሴት ሰንሰለት ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ ያስችላል።
በቴሌ ክላውድ ላይ የሚመሰረተው እና በመጀመሪያው ምዕራፍ በተመረጡ ወረዳዎች ተግባራዊ የሚደረገው ይህ ግዙፍ የግብርና መረጃ ሶሉሽን (Big Data Platform Solution) የክልሉን የተቀናጀ የግብርና እሴት ሰንሰለትን በማዘመን ሁሉንም የግብርና አሰራር ሂደት ደረጃዎችን የሚሸፍን ሲሆን፣ ከግብዓት አቅርቦት ጀምሮ የምርት፣ የግብይትና ስርጭት ፍላጎት ትንተና እንዲሁም የዋጋ ክትትል በማድረግ ዲጂታል ግብይትን ከማሳለጥ ባሻገር የመረጃ አሰባሰብና አስተዳደርን በማሳለጥ በተለይም ከአይ.ኦ.ቲ (IoT)፣ ሳተላይት፣ ሪሞት ሴንሲንግ እና በቦታው ላይ ከሚገኙ ባለሙያዎች የሚገኙ ልዩ ልዩ መረጃዎችን (multiple data) ወደ አንድ የመረጃ ቋት በማምጣት በተቋማት መካከል የመረጃ ልውውጥና ተደራሽነት በማስፋት ለክልሉ ግብርና እሴት ሰንሰለት ማዕከላዊ የመረጃ ማከማቻ እና ትንታኔ (data analysis) ማዕከል ሆኖ የሚያገለግል ይሆናል፡፡
በተጨማሪም የኦሮሚያ ግብርና እሴት ሰንሰለትን በግዙፍ መረጃ በመታገዝ የክልሉን ግብርና ዘመናዊነትን እና ዲጂታል የኢኮኖሚ እድገትን ለማምጣት ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች ያሉት ሲሆን፤ የሀብት አጠቃቀምን ማመቻቸት፣ በቅድመ ትንበያ ሞዴሊንግ አማካኝነት ስጋትን መቀነስ፣ ለታለመላቸው የግብርና ጣልቃ ገብነቶች የፖሊሲ ምክረ-ሀሳቦችን በማቅረብ እንዲሁም ምርትን ከፍላጎት ጋር በማጣጣም የገበያ ግንዛቤዎችን በመፍጠር በዲጂታል የተቀናጀ፣ ዘላቂ እና ቀልጣፋ የግብርና እሴት ሰንሰለት በክልሉ ለመፍጠር ከፍተኛ ፋይዳ ይኖረዋል፡፡
ቀደም ሲል ኩባንያችን ከኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት እና በክልሉ ከሚገኙ በርካታ የከተማ አስተዳደሮች ጋር የተለያዩ ስትራቴጅያዊ የአጋርነት ስምምነቶችን በማድረግ የስማርት ሶሉሽኖችን እና ዲጂታል አገልግሎቶችን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችሉ እና የዜጎችን ህይወት የሚያቀሉ ዘመናዊ እና ዲጂታላይዝድ አገልግሎቶችን በመስጠት ላይ እንደሚገኝ ይታወሳል፡፡
በቀጣይነትም ኩባንያችን ከተለያዩ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት የአስተዳደር ቢሮዎች /መሥሪያ ቤቶች ጋር በተለያዩ ኢኒሼቲቮች ረገድ አጋርነትን ለመፍጠር በንቃት እየተጋ የሚገኝ ሲሆን፣ በተጨማሪም ዲጂታል ሶሉሽኖችን በማቅረብ በክልሉ ያለውን የአሰራር ስርዓት ለማዘመን የቴክኖሎጂ ድጋፉን እና መሰል የአጋርነት ጥረቶችን የበለጠ ለማጠናከር ያለውን ቁርጠኝነት ለመግለጽ ይወዳል።