የኢትዮ ቴሌኮም የ2013 በጀት ዓመት መጀመሪያ መንፈቅ ዓመት የሥራ አፈጻጸም ማጠቃለያ ሪፖርት

የኢትዮ ቴሌኮም የ2013 በጀት ዓመት መጀመሪያ መንፈቅ ዓመት የሥራ አፈጻጸም ማጠቃለያ ሪፖርት

ይህ ሪፖርት ከሐምሌ 2012 እስከ ታህሳስ 2013 ያለውን የኢትዮ ቴሌኮም የስድስት ወራት የሥራ አፈጻጸም የሚገልጽ ነው፡፡

ኢትዮ ቴሌኮም በበጀት ዓመቱ መጀመሪያ የሦስት ዓመት ስትራቴጂና 2013 በጀት ዓመት እቅድ ተግባራዊ ለማድረግ ዝርዝር ተግባራት በማውጣት እና ለውጤታማነቱ አጠቃላይ የተቋሙን ማህበረሰብ በጋራ በማጣመር ኩባንያችን በደንበኞቹ፣ በሠራተኞቹና በአጋሮቹ ዘንድ ተመራጭ ለማድረግ ሰፊ ሥራዎችን ሲያከናውን ቆይቷል፡፡

በበጀት ዓመቱ የተያዙ ስትራቴጂያዊ ግቦችን ለማሳካት መጠነ ሰፊ የለውጥና የማሻሻያ ሥራዎች የተከናወኑ ሲሆን በዋናነትም መጪውን የውድድር ገበያ ታሳቢ ያደረጉ ሰፊ የዝግጅት ሥራዎች፣ የደንበኞች ተሞክሮን ማሻሻልና እርካታን ማሳደግን ታሳቢ ያደረገ የኦፕሬሽን ልህቀት ማምጣት፣ የአገልግሎት ተደራሽነትና ጥራትን ለማሳደግ የሚረዱ መጠነ ሰፊ የፕሮጀክት ሥራዎች ማከናወን፣ የደንበኞችን አቅም ያገናዘበ የታሪፍ ማሻሻያ ማድረግ፣ የቴሌኮም አገልግሎት ፍላጎት ማስተናገድ የሚያስችል የኔትወርክ አቅም የማሳደግ፣ የቢዝነስና የቴክኖሎጂ መናበብ በመፍጠር አዳዲስ አገልግሎቶች ማምጣት፣ የሀብት አጠቃቀም ማሻሻልና የፋይናንስ አቅምን ማጎልበት፣ የገጽታ ግንባታ ሥራዎችን ማከናወን፣ የተቋማችን ሠራተኛና አመራር የማስፈጸምና የመፈጸም እንዲሁም ውሳኔ የመስጠት አቅምንና ክህሎትን ማጎልበት የሚያስችሉ በርካታ ሥራዎች ተከናውነዋል፡፡

የኩባንያችን የአገልግሎት አድማስ ለማስፋት፣ ተወዳዳሪነቱንና ቀጣይነት ያለው እድገት ለማረጋገጥ የሚረዳ የማቋቋሚያ ደንብ ማሻሻያ በሚኒስትሮች ምክር ቤት የተደረገ ሲሆን ይህም የተቋሙን ካፒታል ወደ 400 ቢሊዮን ብር የሚያሳድግ፣ በሞባይል ፋይናንስ ዘርፍና ተያያዥ የዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎቶች ላይ ለመሳተፍ የሚፈቅድ፣ እንዲሁም በሀገርና በዓለም አቀፍ ደረጃ በሌሎች የኢንቨስትመንት ዘርፎች ላይ ለመሳተፍ የሚያስችል እና ኢትዮ ቴሌኮም ዓላማውን ከግብ ለማድረስ የሚረዱ የንግድ ድርጅትን ማቋቋም ጨምሮ ሌሎች ተዛማጅ ስራዎች ማከናወን እንዲችል የሚፈቅድ ነው፡፡ ኩባንያችን የሞባይል ገንዘብ አገልግሎት (Mobile Money) ለመጀመር የሚያስችሉ የዝግጅት ሥራዎች በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡

በተጨማሪም ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ የፈሰሰባቸው የኩባንያችን መሠረተ ልማቶችን በማስፋፋትና በማጠናከር የኔትወርክ ሽፋንና አቅምን ለማሳደግ እንዲሁም መሰረተ ልማቶችን በማከራየት ተጨማሪ የገቢ ምንጭ ለማግኘት እና የአገልግሎት ጥራትን ለማሳደግ የሚያስችሉ አጠቃላይ 137 የፕሮጀክት ሥራዎች በመከናወን ላይ ይገኛሉ፡፡

 

ኩባንያችን ዓለም አቀፍ አማካሪ ድርጅት (KPMG) በመቅጠር የቋሚ ንብረት ግመታ ሥራ ያከናወነ ሲሆን የተቋማችን ሀብት IFRS የሂሳብ አያያዝ ስርዓት መሠረት ከተከናወነ በኋላ አጠቃላይ የሀብት መጠኑ 42 በመቶ አድጓል፡፡

ኩባንያችን በመጀመሪያ መንፈቅ ዓመት 25.57 ቢሊዮን ብር አጠቃላይ ገቢ በማግኘት የእቅዱን 95% አሳክቷል፡፡ ይህ ውጤት ከባለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር 12.3% አድጓል፡፡ይህም የደንበኞች የቴሌኮም አጠቃቀምን ለማሳደግና ተሞክሯቸውን ለማሻሻል የሚስችሉ የኔትወርክ ማስፋፊያ፣ የአገልግሎት ጥራት ማሻሻያ እንዲሁም የደንበኞችን ፍላጎትና ወቅታዊነትን የተላበሱ 21 አዳዲስ እና 18 ነባር የሀገር ውስጥና የዓለም አቀፍ ምርትና አገልግሎቶችን በማሻሻል ለደንበኞች ለማቅረብ በመቻሉ የተመዘገበ ነው፡፡ የተገኘው ገቢ በአገልግሎት አይነት ሲታይ የገቢ ድርሻ የሞባይል ድምጽ 49% ድርሻ ሲኖረው ዳታና ኢንተርኔት 26.3% ዓለም አቀፍ ጥሪ 10.3% እሴት የሚጨምሩ አገልግሎቶች 11% እንዲሁም ሌሎች አገልግሎቶች 3.4% ድርሻ አላቸው፡፡

የውጭ ምንዛሪ ከሚያስገኙ አገልግሎቶች 80.21 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር በማግኘት የእቅዱን 105.3% ያሳካ ሲሆን ካለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር 5.9% እድገት አስመዝግቧል፡፡ ይህ ውጤት ሊመዘገብ የተቻለው አዳዲስ የገቢ ምንጮችን በመተግበርና የውጭ ምንዛሪን የሚያሳጡ የቴሌኮም ማጭበርበር ተግባራትን በተለያዩ ስልቶች በመከላከል፣ የተቋም ደህንነትን ለማረጋገጥ ልዩ ትኩረት በማድረግ እና ዓለም አቀፍ ቢዝነስ አጋሮቻችን ጋር ያለውን ግንኙነት ለማሻሻልና ለማጠናከር ሰፊ ሥራዎች በመከናወናቸው ነው፡፡

ኩባንያችን በግማሽ ዓመቱ ብቻ 16.24 ቢሊዮን ብር ታክስና 500 ሚሊዮን ዲቪደንድ ገቢ በማድረግ የሚጠበቅበትን ኢኮኖሚያዊ አስተዋጽዖ ለመወጣት ችሏል፡፡ በተጨማሪም በቬንደር ፋይናንሲንግ ሞዳሊቲ ለተከናወኑ ፕሮጀክቶች ብድር 4.7 ቢሊዮን ብር ወይም 126.14 ሚሊዮን ዶላር ክፍያ በመፈጸም ከአጋሮቹ ጋር ያለውን መልካም ግንኙነትና ተአማኒነት ማስቀጠል ችሏል፡፡

የደንበኞቻችን ብዛት 50.7 ሚሊዮን የደረሰ ሲሆን ካለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር 11.2% እድገት አሳይቷል፡፡ በአገልግሎት አይነት ሲታይ የሞባይል ድምፅ ደንበኞች ብዛት 48.9 ሚሊዮን የመደበኛ ብሮድባንድ ደንበኞች 309.4 ሺህ የመደበኛ ስልክ ደንበኞች 981 ሺህ እንዲሁም የዳታና ኢንተርኔት ተጠቃሚዎች 23.54 ሚሊዮን ናቸው፡፡ በዚህም አጠቃላይ የሞባይል ኔትወርክ የህዝብ ሽፋን 95% እና የቆዳ ሽፋን 85.4% ሲሆን አጠቃላይ የቴሌኮም ስርጸት (teledensity) 50% ደርሷል፡፡

የኩባንያችን ቀጣይነት ያለው እድገት ለማረጋገጥ የሰው ኃይሉን በእውቀት፣ በክህሎትና በመልካም የሥራ ባህል ከማነጽ አኳያ የተለያዩ የሥልጠና ፕሮግራሞችን በመቅረጽ 8,441 ሠራተኞች ስልጠና እንዲወስዱ ተደርጓል፡፡ የሠራተኛውን ተነሳሽትና የባለቤትነት መንፈስ የሚያሳድጉ ሥራዎች የተከናወኑ ሲሆን ለአብነትም ሠራተኞችን በተቋሙ ስትራቴጂና የሥራ አፈጻጸም ግምገማ ላይ በማሳተፍ ግብዓት እንዲሰጡ የማድረግ፣ የሥራ መገልገያ መሣሪያዎችን አቅርቦት ማሻሻል፣ የሥራ ከባቢን አመቺና ደህነንቱን የማረጋገጥ እንዲሁም የተለያዩ የማበረታቻ ሥርዓቶችን በመተግበር የተሻለ የሥራ ከባቢን የሚፈጥሩ ሥራዎች ተከናውነዋል፡፡

ኩባንያችን 310 ሺህ በላይ ዜጎች የገቢና የስራ ዕድል መፍጠር ችሏል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ የኩባንያችን ምርትና አገልግሎት ለደንበኞች የሚያደርሱ 285 ሺህ በላይ አጋሮች ሲሆኑ ቋሚና ጊዜያዊ ሠራተኞች እንዲሁም ከኩባንያችን ጋር የተለያዩ አገልግሎት የሚሰጡ የቢዝነስ አጋሮቻችንን ይገኙበታል፡፡ በግማሽ ዓመቱ ከቴሌኮም ጋር ተዛማጅ በሆኑ ሥራዎች ተሰማርተው የሥራና የገቢ እድል የተፈጠረላቸው ዜጎች ቁጥር 25 ሺህ በላይ ደርሰዋል፡፡

 ኩባንያችን ለማህበረሰባችን ፋይዳ ባላቸው ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በስፋት በመሳተፍ ማህበራዊ ኃላፊነቱን በተቀናጀ መልኩ በሚገባ እየተወጣ ሲሆን በግማሽ ዓመቱ በአይነት፣ በአገልግሎትና በገንዘብ በድምሩ 322.35 ሚሊዮን ብር በላይ አስተዋጽዖ አድርጓል፡፡ በመላው ሃገሪቱ በጤና፣ በአካባቢ ጥበቃ፣ አረንጓዴ ልማትና ማስዋብ ላይ ተሳትፏል፡፡ በተጨማሪም ሠራተኞቻችን በበጎ ፍቃደኝነት ላይ የተመሠረተ አስተዋፅኦ በማድረግ 3.03 ሚሊዮን ብር የገንዘብና የተለያዩ የቁሳቁስ ድጋፍ እንዲሁም ደም በመለገስና የመልካም ፍቃድ አገልግሎት በመስጠት እጅግ የሚበረታታና አርአያነት ያለው ተግባር አከናውነዋል፡፡

 

በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወቅት የቴሌኮም አገልግሎት ለህብረተሰቡ ያለው በጎ ተጽዕኖ ከፍተኛ በመሆኑ አገልግሎቱ እንዳይስተጓጎል እንዲሁም ሠራተኞቻችን ለኮቪድ-19 ተጋላጭ እንዳይሆኑ ለማድረግ ሰፊ ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራዎች፣ የመከላከያ ቁሳቁሶችንና የትራንስፖርት አገልግሎት ቀርቧል፡፡ ከኮሮና ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ ማህበረሰቡ ከቤቱ ሆኖ ሥራውን ማከናወን እና ማህበራዊ ርቀትን ጠብቆ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴውን ማድረግ እንዲችል የቴሌኮም አገልግሎቶች ላይ ከፍተኛ ቅናሽ ያለው ፓኬጅ ለተጠቃሚዎች ቀርቧል፡፡ በተጨማሪም የኮሮና ቫይረስ ለመግታት ለሚካሄደው ምርምር 16 ሚሊዮን ብር የገንዘብ ድጋፍ በማድረግ፣ የማህበረሰቡን ግንዛቤ ለማሳደግ የስልክ ጥሪን የኮሮና ወረርሽኝን መከላከል መልዕክቶች ለማስተላለፍ መጠቀም፣ የጤና ሚኒስቴርና የማህበረሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ወረርሽኙን አስመልክቶ በድረ ገጻቸው የሚያስተላልፉትን መረጃ ነጻ አገልግሎት በመስጠት፣ በኮቪድ ምክንያት እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው አካላት የሚሆን የገንዘብ ማሰባሰቢያ አማራጮችን የማቅረብና የመሳሰሉ ተግባራት አከናውኗል፡፡

ኩባንያችን በግማሽ ዓመቱ ካጋጠሙት ተግዳሮቶች መካከል ከሰኔ 22 እስከ ሐምሌ 15 ቀን 2012 በመላው ሀገሪቱ በጸጥታ ችግር ምክንያት የኢንተርኔት አገልግሎት መቋረጥ እንዲሁም ከጥቅምት 24 2013 ጀምሮ በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ባጋጠመው ችግር ምክንያት የአገልግሎት መቋረጥ፣ የፋይበርና የኮፐር መስመሮች ስርቆትና መቆራረጥ፣ በተቋም ንብረትና ሠራተኞች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች እና የሃይል አቅርቦት መቆራረጥ በዋናነት የሚጠቀሱ ሲሆኑ የኮሮና ወረርሽኝ መከሰት ለተቋሙ አገልግሎት አሰጣጥ ተግዳሮት ሆነዋል፡፡

በአጠቃላይ የኩባንያችን የግማሽ ዓመት አፈጻጸም በተለይም ዓለማችንና ሀገራችንን ከገጠመው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ እንዲሁም በወቅቱ በአንዳንድ የሀገራችን አካባቢዎች ከነበረው የጸጥታ ችግር አንጻር የቴሌኮም አገልግሎትን ለመስጠትና ለማስፋፋት ካለው ፈታኝ ሁኔታ አፈጻጸሙን እጅግ አመርቂ ያደርገዋል፡፡ ይህን ውጤት ኩባንያችን ሊያስመዘግብ የቻለው የተቋሙ አመራርና ሠራተኞች ኩባንያውን በደንበኞቹና በአጋሮቹ ዘንድ ተመራጭ ለማድረግ ያሳዩት ከፍተኛ ቁርጠኝነት እንዲሁም ላቀዷቸው ግቦች መሳካት ባደረጉት የተቀናጀ ጥረትና የነበሩት አስቸጋሪ ሁኔታዎችን (Crisis) በብቃት በመምራታቸው ነው፡፡

በመጨረሻም ለተመዘገበው አመርቂ አፈጻጸም ለደንበኞቻችን፣ ለሥራ አጋሮቻችን እና ለባለድርሻ አካላት ምስጋናችንን እናቀርባለን፡፡ 

Share This Post:

Share on facebook
Share on telegram
Share on twitter
Share on linkedin

Follow Us

Recent Posts

Archives